በኢ.ሶ.ክ.መ.በመቀመጫ ጅግጅጋ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት ጉዳዮች ቅርንጫፍ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ (cakaaranews)አርብ፤ ሚያዚያ 13/20010 ዓ.ም የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ በኢትዮጵያ ሶማሌ፤በሌሎች ሁለት ክልሎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሊከፍት መሆኑን እና የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ለሃገር ውስጥ ሚዲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። የፓስፖርት አገልግሎት ፈልገው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸው የተቋሙ ዋና ዳይረክቴር  በመግለጫው ላይ አብራርቷል። ይህንን አሰራር ቀልጣፋ ለማድረግ መምሪያው ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ በየክልሎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በመክፈት ዜጎች በየአካባቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማረግ ነው።

የኢፌዴሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገ/ዮሃንስ ተክሉ አዲስ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ እስከ ግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ድረስ ተከፍቶ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስታውቋል። በተጨማሪም በአዳማ እና ሰመራ ከተሞችም በተመሳሳይ ወቅት አዳዲስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እንደሚሰጡም ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል። ከአሁን በፊት አዋሳ ፣ ባሕር ዳር እና መቀሌን ጨምሮ በ6 ክልሎች ቅርንጫፎች ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም አቶ ገ/ዮሃንስ ጠቁመዋል። ነገር ግን ‘’አዲስ አበባ ያለው ነው ትክክለኛ ፓስፖርት የሚሰጠው’’ በሚል የተሳሳተ መረጃ በህገወጥ ደላሎች በማሰራጨት ዜጎች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡም ተናግረዋል።

ይህ የተሳሳተ መረጃ መሆኑንም የሚሰጠው ፓስፖርት በሁሉም ቅርንጫፎች አንድ ዓይነት በመሆኑ ዜጎች የሚከፈቱትን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጨምሮ በየአካባቢያቸው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በተመሳሳይ የክፍያ ፎርም መሙላትና ቀጠሮ ማስያዝ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አዲስ አሰራር የጀመረ ሲሆን የሙከራ ጊዜው እንዳለቀ ወደ ሥራ የሚገባ በመሆኑ ይህንንም አገልግሎት ዜጎች በአካባቢያቸው ካለው ንግድ ባንክ ማግኘት ይችላሉ ብለዋል። መምሪያው በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 6ሺህ ባለጉዳዮችን እያስተናገደ ይገኛል። ተገልጋዮች ለሚያነሷቸው ማንኛውም ዓይነት ቅሬታዎች በ8133 ነጻ የስልክ ጥሪ መግለጽ እንደሚችሉም ተጠቁሟል።