1ኛው የኢ.ሶ.ክ.መ የባህል ሳምንት ፌስቲቫል በጅግጅጋ ተጠናቀቀ

 ጅግጅጋ(cakaaranews) እሁድ ፤ ሚያዝያ 21/2010 ዓ.ም ለአንድ ሳምንት ያህል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና በጅግጅጋ በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የኢ.ሶ.ክ የባህል ሳምንት ፌስቲቫል ዛሬ ባማረና በደመቀ ሁኔታ ተጠናቀቀ። በፌስቲቫሉ ስድስት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከተማ አስተዳደሮችና የሺኒሌ ወረዳ ባህል ባንዶች በተለያዩ  የሶማሌ ብሔርሰብ ባህላዊ ጭፈራዎች ፣ ባህላዊ ምግብ አሰራር ፣ የባህላዊ ቤት አሰራር እና በባህላዊ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ውድድር የተካሄደ ሲሆን በሥነ-ስርዓቱ ላይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዙሪያ የተደረገ የሲምፖዝየም ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበዋል።

በተጨማሪም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ፉኣድ አህመድ ጃማ ዛሬ በበዓሉ መዝጊያ በተጠናቀቀው መለስ ዜናዊ ፓርክ ላይ እንደተናገሩት “ይህ ለአንድ ሳምንት ያህል በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ሶማሌ የባህል ሳምንት ፌስቲቫል በክልል ደረጃ ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ብለዋል። በፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ  የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔርሰብ ባህላዊ ጭፈራዎች ፣ ባህላዊ የምግብ አሰራር ፣ የሶማሌ ባህላዊ ቤት አሰራር እና በባህላዊ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ውድድር በባህል ቡዱኖች መካከል መካሄዱን እና ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና ከብሔራዊ ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሶማሌ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዙሪያ የተደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎች በሲምፖዚየም መልክ መቅረቡንም ቢሮ ኃላፊው አክሏል።

አያይዘውም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ደረጃ የተከበረው የኢትዮጵያ ሶማሌ የባህል ሳምንት ፌስቲቫል  የክልሉ ህዝብ ባህላዊ ቅርሶችና የቱሪዝም መዳረሻዎችን አቅም ለማጠናከር ለማልማት ለማስተዋወቅና የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ባህላዊ ቅርሶች ጠብቆ በማቆየት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሆኑንም አቶ ፉኣድ አህመድ ገልጸዋል።

የበዓሉ ተሳታፊዎችና የክልሉ ባህል ቡዱኖች በበኩላቸው በክልላቸው የባህል ሳምንት በክልል ደረጃ መዘጋጀቱን የክልሉ መንግስት ለባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ከመሆኑም ባሻገር በሶማሌ ብሔረሰብ ባህላዊ ጭፈራዎች ፣ ባህላዊ የምግብ አሰራሮች ፣ ባህላዊ ቤት አሰራር(አቀል ሶማሊ) እና በባህላዊ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ዙሪያ በመወዳደራቸው እጅግ በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በጅግጅጋ ከተማ የተከበረውን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባህል ሳምንት የክልሉ 6 ከተማ አስተዳደሮችና የሺኒሌ ወረዳ ባህል ቡዱኖች የተሳተፉበት ሲሆን በ2008 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ  በጅግጅጋ መከበሩ ይታወሳል።