የኢ.ሶ.ክ መንግስት በቀላፎ ወረዳ በዋቢሸቤሌ ውሃ መጥለቅለቅ ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የምግብ ድጋፍ አደረገ

ቀላፎ(cakaaranews)ቅዳሜ᎓ሚያዝያ 27/2010ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሸቤሌ  ዞን ቀላፎ ወረዳ በዋቢሸቤሌ ወንዝ ዳርቻ ይኖሩ የነበሩ አባወራዎች በቅርቡ በወንዙ መሙላት ምክንያት በተከተለው የጎርፍ ማጥለቅለቅ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ፣ የተለያዩ የቤት መገልገያ ቁሳቁስ እና የመጠለያ ሸራዎችን ድጋፍ ማድረጉን የቀላፎ ወረዳ አመራር አስታውቋል።

በተያያዘም ለተረጅዎቹ የተደረገላቸውን እርዳታና ድጋፍ አስመልክቶ ለክልሉ ሚዲያ አውታሮች ማብራሪያ የሰጡት የቀላፎ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው ተጠባባቂ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ኡመር አህመድ የክልሉ መንግስት በቅርቡ የዋቢሸቤሌ ወንዝ መሙላትን ተከትሎ በተፈጠረው የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አባወራዎች የተለያዩ የምግቦች አይነቶች እንደ ሩዝ ፣ ስንዴ ፣ ስኳር እና የምግብ ዘይት እንዲሁም የተለያዩ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች እና የመጠለያ ሸራዎችን ድጋፍ አድርገዋል ብሏል። በተጨማሪም ለተጎጂዎቹ የተደረገላቸው ድጋፉ ወቅቱን የጠበቀና በአስፈላጊው ጊዜ የተደረገ ፈጣን ምላሽ መሆኑንም ሃላፊው አክሏል።

በሌላ በኩል በሸቤሌ ዞን የቀላፎ ወረዳ ጸጥታና ፍትህ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጀውሀር ሙሁመድ ሙሴ በቀላፎ ወረዳ በአለው ኢጋርሲ ደበከቱር ቀበሌዎች እና በሌሎች ንዑስ ቀቤሌዎች የሚኖሩና በጎርፉ አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ማህበረሰብን የክልሉ መንግስት ለተጎጂዎቹ የላከላቸው የተለያዩ የምግብ ነክ እና የቤት መገልገያ ቁሳቁስ እቃዎች ማከፋፈላቸውን ገልጿል። አያይዞም የመንግስት እርዳታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በአስፈላጊ ወቅት በአግባቡ ማድረሳቸውንም አቶ ጀውሀው አስገንዝቧል።

በመጨረሻም በጎርፉ የተፈናቀሉና ድጋፍ የተደረገላቸው አባወራዎች ወቅቱን ጠብቆ በአስፈላጊው ጊዜ በክልሉ መንግስት በተደረገላቸው የተለያዩ እርዳታዎች እና የአልሚ ምግቦች ድጋፍ ደስታኛ ከመሆናቸውም ባሻገር ለክልሉ መንግስት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።