በም/ርዕሰመስተዳደር የሚመራ የክልል ከፍተኛ አመራር ልዑኳን ቡዱን ከዋርዴር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድረጉ

ዋርዴር(Cakaaranews)ቅዳሜሚያዚያ 27/2010..  በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ም/ፕሬዝዳንትና የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሱኣድ አህመድ ፋራህ የሚመራ ከፍተኛ የክልል አመራር ልዑኳን ቡዱን፣ የዶሎ ዞን መቀመጫ በሆነችው ዋርዴር ከተማ ሲደርሱ  ህብረተሰቡ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡ከልዑኳን ቡዱኑ መካከል የክልል ም/ቤት አባለት፤ቢሮ ሃላፊዎች፤ዳይረክተሮች፤ሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባላሙያዎችም ይገኙበታሉ።

በዚህ መሰረት ልዑኳን ቡዱኑ በወርዴር ወረዳ አከባቢዎች የተከናወኑትን የመሰረተ ልማት አውታሮች፣ የወርዴር ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ እንዲሁም የክልሉ መንግስት የልማት እቅዶች አካል የሆኑትን የዉሃ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የእንስሳት መኖ የክንውን ተግባራትን የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ከአቀባበሉና ከመስክ የስራ ጉብኝቱ በኋላ በም/ፕሬዝዳንቷና የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ  ክቡርት ሱኣድ አህመድ ፋራህ የሚመራው ልዑኳን ቡዱኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የዋርዴር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም በዋርዴር ከተማ የተከናወኑት የመሰረተ ልማት አውታሮችን እንደ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ የዋርዴር ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ፣ የመጠጥ ዉሃ ጉድጓዶች እና የመሳሰሉትን የልማት ስራዎች እንደተከናወኑ  ም/ፕሬዝዳንቷ  አስመስክረዋል፡፡ አያይዞም ም/ፕሬዝዳንቷ  በአሁኑ ጊዜ በዋርዴር ከተማና በአጠቃለይ በክልሉ የተመዘገበዉን የልማትና የሰላም ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ክልሉ በምግብ ዋስትና ራሱን ችሎ ህብረተሰቡ አምራች ሀይል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢ.ሶ.ክ የሠረተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዲወሊ መሀመድ ፋራህ በበኩላቸው ክልሉ ከዚህ በፊት  ያሳለፋቸዉን በርካታ ውጣ ውረዶችን በማውሳትና በአሁኑ ጊዜ ክልሉ የሰላም᎓የልማትና ዲሞክራሲ ስኬቶችን በማስመዝገብ በክልሉ መንግስት የተከናወኑት ዘርፈብዙ የልማት ድሎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በውይይቱ ላይ ለታደሙት የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪዉን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻ የውይይቱ ታዳሚዎች በዋርዴር ወረዳና በዶሎ ዞን የክልሉ መንግስት ያከናወናቸዉን የልማት ስራዎችን በማድነቅ በክልሉ የተመዘገበዉን የሰላምና ጸጥታ ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከክልሉ መንግስት ጎን ቆመው የድርሻቸው እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡